Welcome

የ'አዲስ:ዜና'ን መተግበሪያ ያውርዱ

የተሻለ የንባብ ተሞክሮ ለማግኘት እና የቅርብ ጊዜ ዜናዎችን ለማየት መተግበሪያውን ያውርዱ።!

Download
Cancel
Image:AddisZena
አዲስ ዜና | Addis Zena
“ዕድሉ ቢሰጠን ኢትዮጵያዊ ግብ ጠባቂዎች ጠንካሮች ነን…” ፋሲል ገ/ሚካኤል /ባህርዳር ከተማ/

ወደኋላ ልመልሳችሁና የዛሬ 8 አመት በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አመራርነት ዋሊያዎቹ ለደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ዋንጫ ያለፉበትን ጊዜ ላስታውሳችሁ….. ያኔ ከ31 አመት በኋላ ወደ መሠረትነው የአፍሪካ ሰላማዊ ጦርነት ስንመለስ የዛሬ እንግዳዬ ትልቅ ደስታ ከተሰማቸው ኢትዮጵያዊያን አንዱ ነው ጭራሹኑ ኳሱ ውስጥ የለም ጨዋታውን ሲኒማ ቤት ውስጥ እንኳን ማየት የተከለከለ ታዳጊ… በአጥር ዘለው ጨዋታውን ለማየት ከታደሉ ታዳጊዎች መሃል አንዱ የሆነው እንግዳችን…ዛሬ ግን አገሩን ለማኩራት ታሪክ ከሰሩ ጋር ስሙን እኩል ለማስቀመጥ እየተንደረደረ ያለ ወጣት ነው…..ይህ ወጣት የዋሊያዎቹን በር ለረጅም አመታት ይጠብቃል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ባለፈው ማክሰኞ ኢትዮጵያ ባህርዳር ላይ ዚምቧብዌን ስታሸንፍ የውበቱ አባተ ስብስብን በር ጠብቆ በጀግንነት ያላስደፈረ ግብ ጠባቂ ነው በሰበታ ከተማ ያሰለጠነውን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱን ተከትሎ ባህርዳር ከተማ የከተመው ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ነው… ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ከድሉ በኋላ የስልክ ቆይታ ያደረገው ግብ ጠባቂው ለቀረቡለት ጥያቄዎች የሰጠው ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል….

ሀትሪክ:- ባለቀ ሰአት በተቆጠረ ግብ ዚምቧብዌን 1 ለ ዐ ረታችኋልና….እንኳን ደስ አለህ?

ፋሲል:- እንኳን ደስ አለን በተገኘው ድል ደስ ብሎኛል በተለይ ከጋና ሽንፈት በኋላ ወደ ድል አድራጊነት የተመለስንበት ተስፋ የሰጠን ድል በመሆኑ ደስ የሚል ስሜት ተሰምቶኛል

ሀትሪክ:- ዛሬ የደረስክበትን ስታይ በዚህ ፍጥነት የአገሬን ብሄራዊ ቡድን አገለግላለሁ ብለህ ጠብቀሃል..?

ፋሲል:- /ሳቅ/ በፍጹም….ካለው ሂደት ሲታይ በዚህ ወጣትነቱ አገርን የወከለ የለምና በፍጹም አልጠበኩም ነገር ግን ይህን ታሪክ የመቀየር ህልም ነበረኝና ተግቼ ሰርቻለሁ እግዚአብሄር ይመስገንና ህልሜ በመሳካቱ ደስ ብሎኛል እድለኛም ሆኔ በጥሩ አሰልጣኞች እጅ በማደጌም እነርሱን ማመስገን እፈልጋለሁ። ማንም ጠንክሮ ከሰራና በአሰልጣኙ ታምኖበት እድሉን ካገኘ የማይቻል ነገር የለም ብዬ አምናለሁ

ሀትሪክ: እነኚህ ምስጋና የተሰጣቸው አሰልጣኞች እነማን ናቸው….?

ፋሲል:- አሰልጣኝ ውበቱ አባተና አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ናቸዋ..

ሀትሪክ:- እስቲ ስለተፋላሚዎችህ ጀማል ጣሰውና ተክለማርያም ሻንቆ አውራኝ…?

ፋሲል:- ለዋሊያዎቹ ከተመረጥኩ ጀምሮ ሁለቱም በደንብ ነው የረዱኝ የራስ መተማመኔን ጨምረውልኛል ከጎኔ ናቸውና ማመስገን እፈልጋለሁ ሁለቱም ተፎካካሪዬ አይመስሉኝም በደንብ አግዘውኛል ቀረቤታና አቀራረባቸው የተለየ ነው ውስጣቸው ቅን ነው ጎሜዝ ተክቼው ስገባ አበረታቶኛል በዚህ በኩል እድለኛ ነኝ ለሀገራችን ይሄ ህብረት ወሳኝ መሆኑ ገብቶን እየሰራን ነው

ሀትሪክ:- ለዚህ ነው ከጋና ጋር በነበረው ጨዋታ ተቀይረህ ልትገባ ስትል የጀማል ድጋፍ ለየት ያለው..?

ፋሲል:- /ሳቅ/ በቃ እንደሱ ነው…. የመጀመሪያዬ እንደመሆኑ አቅም እንዳለኝና ይዣቸው እንደምወጣ እንደሚተማመን ነግሮ ውስጤን አጠንክሮኝ ነው የገባሁት…በአጠቃላይ ሁለቱንም አመሠግናለሁ

ሀትሪክ:- ጨዋታው ሲያልቅ ውስጥህ ምን አለ..?ምንስ ተሰማህ…?

ፋሲል:- ድሉ አጨራሱ ብዙ ነገር ያሳስባል በጣም ነው የተደሰትኩት ነገር ግን ከጨዋታው በፊት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ድሉ ለሀገራችን ወሳኝ ነው በተለይ በአል እንደመሆኑ ማሸነፍ እንዳለብን የነገረንን ነው ያስታወስኩትና የተደሰትኩት… አዲስ አመት ከቀናት በኋላ ይገባልና ለመላው ኢትዮጵያዊ እንደ በዓል ስጦታ ይቆጠረልኝ ለማለት ነው..በአገር ደረጃ ካለው ቀውስና መከፋፈል አንጻር ህዝቡን አንድ የሚያደርገው ኳሱ ነውና በድሉ ደስ ብሎኛል.. የተሻለ የተለወጠ እውነተኛ አዲስ አመት ይሁንልን ብያለሁ

ሀትሪክ:- ወደ ኋላ ልመልስህና…ሰፈር ስትጫወት ምርጫህ ግብ ጠባቂ ነበር…?

ፋሲል:- እውነት ለመናገር ትምህርት ቤት እያለሁ ቅርጫት ኳስና እግር ኳስ እሞክር ነበር ነበር …ደብረ ሰላም በተሰኘው የካቶሊክ ትምህርት ቤት በቅርጫት ኳስ ትምህርት ቤቱን ወክዬ ሁሉ ተጫውቻለሁ… በኋላ ላይ ዳሽን ቢራ ፕሪሚየር ሊጉን ሲቀላቀልና ታዳጊ ቡድን ሲይዝ እኔም ገባሁ…አሰልጣኙ ተገኘ እቁባይ ቅርጫት ኳስ ስጫወት ያውቀኝ ነበረና ወደ ግብ ጠባቂነት ብትመጣ ይሻላል ብሎ አበረታቶ የግብ ጠባቂነቱ ህይወቴ መነሻ ሆኖኛል በት/ቤቱ ፕሮጀክት ላይ ታቅፌ እያለ የስፖርት አስተማሪያችን ስለሚያውቀኝ ያንተ ቦታ ግብ ጠባቂነት ብሎ አሳመነኝና ይኸው ህይወቴ ሆኖ ቀረ…

ሀትሪክ:- እስቲ አጠር አድርገህ ፕሮፋይልህን ንገረኝ..?

ፋሲል:- ዳሽን አንድ አመት ነው የተጫወትኩት በመጣበት አመት ሲወርድና ሲፈርስ በቢጫ ቲሴራ ወደ ደደቢት አቀንቼ አንድ አመት ተጫወትኩ… እነ አይናለም ሃይለና አስራት መገርሳ በገንዘብ ምክንያት ክለቡን በለቀቁበት አመት ደደቢትን ትቼ ወደ አክሱም ከተማ ሄድኩ… አንድ አመት እንደ ተጫወትኩ አሰልጣኝ ውበቱ ወደ ሰበታ ከተማ አመጣኝ የሰበታ ከተማ ቆይታዬ በፕሪሚየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጫወት እድል ያገኘሁበት ነው ሰበታ አንዱን አመት በውበቱ አንደኛውን ደግሞ በአብርሃም ስር ተጫውቼ ለ2014 እና 2015 ደግሞ ለባህርዳር ከተማ ለመጫወት ፊርማዬን አኑሬ አመቱን እየጠበኩ እገኛለሁ

ሀትሪክ:- ሰበታ ከተማዎች ውልህን ለማደስ አልፈለጉም.. ወይስ አሰልጣኝ አብርሃምን ላለመለየት ለባህርዳር ከተማ ፈረምክ…?

ፋሲል:- ሲጀመር ውሌን ለማደስ አላቀድኩም.. በአንዳንድ ነገሮች አልተስማማንም ነበርና ለመልቀቅ በመወሰኔ አሰልጣኝ አብርሃም እንደሚፈልገኝ ሲነግረኝ ሁለቴ ማሰብ አላስፈለገኝም በተቻለ መጠን ጥሩ ጊዜ እንደሚኖረኝ ተስፋ አደርጋለሁ

ሀትሪክ:- ለቋሚ አሰላለፉ ፉክክር ራስህን እያዘጋጀህ ነው..?

ፋሲል:- /ሳቅ/ በባህር ዳር ከተማ ጥሩ ቡድን እንደሚኖረን ተስፋ አደርጋለሁ ከኔ ውጪ ጥሩ አቋም ላይ ያለው አቡቡከር ኑሪም አለ ሌሎች በረኞችም አሉ ከነርሱ ጋር ጠንካራ ፉክክር አደርጋለሁ ብዬ አምናለሁ አሰልጣኝ አብርሃም በወቅታዊ አቋም የሚያምን በመሆኑ በባህርዳር ከተማ የተሻለ ተመራጭ ለመሆን እጥራለሁ በኛ የቋሚ ተሰላፊ ፉክክር ቡድናችን ይጠቅማል ብዬ አምናለሁ

ሀትሪክ:- በዳሽን ጥሩ ጊዜ ነበረህኮ…

ፋሲል:- አዎ ወልዲያ ላይ በነበረው የውስጥ ውድድር ጎንደርን ወክለን ምንም ጨዋታ ሳንሸነፍም ሆነ አቻ ሳንወጣ ውድድሩን በአሸናፊነት ጨረስን ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብዬም ተሸለምኩ… ከዚያ በኋላ ነው አድጌ መሻሻል እያሳየሁ አሁን ያለሁበት ቦታ የተገኘሁበት ጎንደር ተወልጄ እንደማደጌ እንደ ግብ ጠባቂ ሞዴል አልነበረኝም ዋና ተምሳሌቶቼ ወደ ውጪ ኳስ ያዘነበለ ነው.. የጁቬንቱሱ ጂያን ሉዊጂ ቡፎን፣ የባየር ሙኒኩ ማኑኤል ኑኤርና የማን.ዩናይትዱ ዴቪድ ደሂያ ናቸው

ሀትሪክ:- እነሱን በደንብ ትከታተላለህ..?

ፋሲል:- በእነሱ ልክ ነው ራሴን የማየው እዚያ ደረጃ ነው ለመድረስ የምጥረው…የውጪ ኳስ ደስ ይለኛል እከታተላለሁ እንደ ግብ ጠባቂ ጨዋታቸው አያመልጠኝም….ልምምድ እንኳን ስሰራ የነርሱን የቪዲዮ ልምምድ እያየሁ ነው.. በደንብ እየተማርኩባቸው ነው.. ከሶስቱ ደግሞ የተሻለ ማኑኤል ኑኤር ኳስ ሲያድንና በእግሩም የሚጫወት መሆኑ እንድመርጠው አድርጎኛል

ሀትሪክ:- አንተስ እንደዛ ነህ?

ፋሲል :- አዎ..መጫወት የምፈልገውም እንደነሱ ነው የተከላካይን ጫና ማቅለል እፈልጋለሁ ኳስ ስናገኝ እንደ ግብ ጠባቂ ሳይሆን እንደ ተጨዋች መጫወት ነው የምፈልገው…

ሀትሪክ:- በረኛ ተጨዋች ነው ከሚለው የካሳዬ አስተሳሰብ ጋር ተመሳሰለብኝ….ልክ ነኝ?

ፋሲል:- አዎ…/ሳቅ/ .እንደዛነው የማምነው የውበቱ የአብርሃምና የካሳዬ አሳብም ይቀራረባልኮ…ፕሪሚየር ሊጉ ባለቀበት ሰአት ካሳዬና አብርሃም የሰበታና የቡና ተጨዋቾችን ሰብስበው እረፍታችንን እንዴት ማሳለፍ እንዳለብን ትምህርት ሰጥተውናል ሃሳባቸው አቋማቸው ተመሳስሎብኛል…

ሀትሪክ:- የውጪ ግብ ጠባቂ ይምጣ ወይስ ይቅር..? አንተ የቱ ጋር ነህ..?

ፋሲል:- የውጪ ግብ ጠባቂ አይምጣ ከሚሉት ነኝ ምክንያቱ ደግሞ በልጠውን የምንማርባቸው ብዙ አይደሉም….አሰልጣኝም ሆነ ደጋፊው የሚሰጣቸው ግምት ካልሆነ በስተቀር የትኛውም ግብ ጠባቂ በአሰልጣኙ ታምኖበት ቢሰለፍ አይከብደውም የሚያስፈልገው እምነቱ ብቻ ነው… አሁን ደግሞ ጎበዝ በረኞች ብቅ እያሉ ነው ካቻምና የነበረውን ስናይ አንድ መከላከያ ብቻ የውጪ ዜጋ ያልሆነ በረኛ የነበረው… እኛም በርትተን ራሳችንን ለማሳየት እየጣርን ነው የውጪ ዜጋ የሆኑ ግብ ጠባቂዎች መምጣት በርትተን እንድንሰራ አድርጎናል.. የውጪ ግብ ጠባቂዎች ቢመጡም ባይመጡም ችግር አለ ብዬ አላምንም አሰልጣኞቻችን ወቅታዊ አቋም ብቻ አይተው ቢያሰልፉ ደስ ይለኛል..ያኔ የውጪ ግብ ጠባቂ ማምጣት ልክ አለመሆኑን ይረዳሉ ብዬ አስባለሁ። ዕድሉ ቢሰጠን ኢትዮጵያዊ ግብ ጠባቂዎች ጠንካሮች ነን….

ሀትሪክ:- አሰልጣኞች ላይም ችግር አለ ለወጣት ዕድል አይሰጡም የሚሉ አሉ…እዚህ ላይ ምን ትላለህ…?

ፋሲል:- አሰልጣኞች እኛን በደንብ የማያዩት ከኛም ችግር ይመስለኛል…ጠንክረን ሰርተን እነሱን ማሳመን አለብን ከአሰልጣኙ ውጪ ተጨማሪ ስራ መስራት አለብን እነሱ የሚበልጡን በዚህ ነው…ሁሌ ተስፋ ሳንቆርጥ ልንታገል ይገባል ያኔ እድል ይሰጡናል ባገኘነው እድልም መጠቀም ከኛ የሚጠበቅ ይሆናል…

ሀትሪክ:- ከውጪ በረኞች ለመማርያነት ይጠቅማል ጥሩ ነበሩ የምትለው እነማንን ነው..?

ፋሲል:- በ2013 ላይ ባይኖሩም የመቀለ 70 እንደርታው ፊሊፖ ጎሮና የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሮበርት ኦዶንካራ ለኛ ትምህርት ሰጪ ነበሩ ብዬ አምናለሁ አሁን በሊጉ ከነበሩት የሰበታ ከተማው ዳንኤል አጄም ምርጫዬ ነበር ዳንኤል አጄ በሰበታ ከተማም አብረን ስንጫወት እንድማርበት አድርጎኛል…

ሀትሪክ:- በክለቦቻችን ትክክለኛ ግብ ጠባቂ የለም በብሄራዊ ቡድን ብቻ ነው የሚገኘው ይባላል…ገጥሞሃል..?

ፋሲል:- በግሌ አልገጠመኝም እድለኛ ነበርኩም በዳሽን ቢራ ስጀምር አዳሙ ንሞሮ ነበር የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ..ተጫውቶ ስላለፈ ምርጥ ስልጠና ሰጥቶኛል …በሰበታ ከተማም አግኝቼዋለሁ… ወደ ዋሊያዎቹ ስመጣ ረጅም ጊዜ የዋሊያዎቹ ግብ ጠባቂ የነበረው ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስን አግኝቻለሁ…ጥሩ ጥሩ አሰልጣኞች ገጥመውኛል እግዚአብሄር ይመስገን .. በሌሎች ክለቦች ጋር ተመሳሳይ ነገር የለም የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ላይ ትኩረት ያንሳልና ሊታሰብበት ይገባል…

ሀትሪክ:- በአሁኑ ወቅት ጥሩ የራስ መተማመን አለኝ ብለህ ታምናለህ…?

ፋሲል:- አዎ በሚገባ የራስ መተማመን አለኝ..አሰልጣኙ የሚለኝና የሚጨምርብኝ መተማመን ያስደስታል ቀጣይ ጊዜያቶቼ የተሻለ እንደምሆንባቸው ርግጠኛ ነኝ

ሀትሪክ:- ከ2008 ጀምሮ ባሉት ስድስት አመታት ምርጡ ጊዜህ መቼ ነው..?

ፋሲል:- በሰበታ ከተማ ያሳለፍኳቸው ሁለት አመታት ምርጡ ጊዜያቶቼ ናቸው… በትልቅ ደረጃ የተጫወትኩት ሰበታ በመሆኑ ምርጡ ጊዜዬ ነው… ለአክሱም ስጫወት ጥሩ ስለነበርኩ አሰልጣኝ ውበቱ አይቶኝ ለሰበታ እንድጫወት አድርጎኛል..በሰበታ ከተማ ጥሩ ጊዜ በማሳለፌ ራሱ አሰልጣኝ ውበቱ ለዋሊያዎቹ ሊጠራኝ ችሏል

ሀትሪክ:- እንደ ግብ ጠባቂ ካንተ ፊት ቢኖሩ የምትመኛቸው ተከላካዮች እነማን ናቸው…?

ፋሲል:- ያለ ጥርጥር እድለኛ ነኝ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ሁለቱም ከፊቴ ናቸው….ያሬድ ባዬና አስቻለሁ ታመነ ምርጫዎቼ ናቸው ከስጋት ነጻ አድርገው በራስ መተማመን ጨምረውልኛል በነሱ እምነት አለኝ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚገርም መግባባትና መናበብ አሳይተናል

ሀትሪክ:- በፕሪሚየር ሊጉ እንደ አጥቂ አስቸጋሪ የምትለው ማንን ነው..?

ፋሲል:- አቡበከር ናስርና ጌታነህ ከበደን ነው የምጠራው…

ሀትሪክ:- ፕሮፌሽናል የመሆን እድል አልነበረም?ወደፊትስ ተስፋው ምንድነው..

ፋሲል:- ዕድሉ ነበር ሙከራም አድርጌ ነበር በተለይ ከስፔን 3ኛ ዲቪዚዮን አንድ ክለብ እድል አግኝቼ ከ23 አመት በታች ውድድር ላይ ስለነበርን ሳይሳካ ቀርቷል አሁንም ነገሮች ተሳክተውልኝ ውጪ የመጫወት እድል እንደማገኝ ተስፋ አደርጋለሁ ህልሜም ነው አሁን ደግሞ በዲ ኤስቲቪ መታየቱ ለብሄራዊ ቡድን መጫወቴ ጥሩ እይታ ይፈጥራልና ዕድሉን እንደማገኝ ርግጠኛ ነኝ እንደ ሀገር ብሄራዊ ቡድኑ መሻሻል እያሳየ በመሆኑ እይታው እንደሚጨምር ተስፋ አደርጋለሁ

ሀትሪክ:- ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ እሄዳለሁ ብለህ ታምናለህ.?

ፋሲል:- በርትቼ ከሰራሁ ለምንድነው የማልሄደው..?/ሳቅ/ የሚጠበቀው መበርታት ብቻ ነው ነገን ሳስብ ሞራል ነው የሚሆነኝ በቀጣዮቹ ጊዜያት ያለብኝን ክፍተት አስተካክዬ ለአፍሪካ ዋንጫው ዝግጁ መሆን እፈልጋለሁ እናም ተስፋ አደርጋለሁ

ሀትሪክ:- ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ 2013 ከባድ አልነበረም…?

ፋሲል:- በጣም ከባድ አመት ነበር ምክንያቱ ኮቪድ ኳሱ ላይ የነበረው ተጽእኖ ከፍተኛ መሆኑ ታይቷል ጨዋታም አስቁሞናል በተለይ ደግሞ በረኛ ላይ ተጽእኖው የሰፋ ነበር ከዚያ ውጪ ምርመራው ሲካሄድ እንደ ግልም እንደ ቡድንም አለባችሁ እየተባለ ትልቅ ፈተና ገጥሞን ነበርና ጫናው ያስታውቅ ነበር አሁንም ስርጭቱ እንደቀጠለ በመሆኑ ህብረተሰቡ ማክስ በማድረግ በመታጠብና ርቀትን በመጠበቅ ራሱን ከኮቪድ እንዲከላከል ጥሪ አደርጋለሁ እግዚአብሄርም ከኮቪዱ ጥቃት እንዲጠብቀን እመኛለሁ

ሀትሪክ:- ለሀገርህ ምን ትመኛለህ..?

ፋሲል:- ለመላው ኢትዮጵያዊያን እውነተኛ አዲስ አመት ይሁንላችሁ….የአመት ለውጡ በሁሉም ዘርፍ ለውጥ የሚታይበት እንደሚሆን አምናለሁ….ሁሉ ነገር መልካም ሆኖ ህዝቡ በአንድ መንፈስ የሚኖርበት ሞት የሚቀርበት ጦርነት አልባ አመት እንዲሆን እመኛለሁ

ሀትሪክ:- ምን ያዝናናሃል…?

ፋሲል:- ፊልም ማየት ደስ ይለኛል ያዝናናኛል በዋናነት ግን መጽሃፍ ማንበብ ያስደስተኛል መጽሃፍ በጣም እወዳለሁ..እዚህ ላይ ጦርነት እንደማይጠቅም ዋጋ ከማስከፈል ውጪ ትርጉም እንደሌለው ማሳያ የሆነ መጽሃፍ ካልከኝ “ኦሮማይ” ምርጥ ማሳያ ነው…

ሀትሪክ:- ጨረስኩ…የመጨረሻ የምታመሰግነው ካለ..?

ፋሲል :- የቅድሚያ ምስጋናው ለእግዚአብሄር ይሁንልኝ ..ከጎኔ ያልተለየችኝ ድንግል ማርያምንም አመሠግናለሁ… ቤተሰቦቼን፣ ላሰለጠኑኝ አሰልጣኞች በተለይ አሰልጣኝ ውበቱ አባተና አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱን አመሰግናለሁ..በሁለቱ ትልልቅ አሰልጣኞች ስር መሰልጠኔ እድለኛ መሆኔን ያሳያል ከታዳጊነት ላሰለጠኑኝ ለተገኘ እቁባይና አዳሙ ንሞሮ፣ ይታገሱ ጓደኞቼን ጨምሮ አመሠግናለሁ… ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም አዲስ አመት ብያለሁ….

logoHatrickSport rc2 cc0
Copyright © All rights reserved | Marvellous LLC