Welcome

የ'አዲስ:ዜና'ን መተግበሪያ ያውርዱ

የተሻለ የንባብ ተሞክሮ ለማግኘት እና የቅርብ ጊዜ ዜናዎችን ለማየት መተግበሪያውን ያውርዱ።!

Download
Cancel
Image:AddisZena
አዲስ ዜና | Addis Zena
የሠሜን ወሎና የዋግ ኸምራ ነዋሪዎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸው ተነገረ

የህወሓት አማጺያን በያዟቸው የሠሜን ወሎና ዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን የአካባቢው ተወላጆች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በአካባቢዎቹ ስላለው ሁኔታ በዝርዝር ለማወቅ አዳጋች መሆኑን የተናገሩት ግለሰቦች በተጠቀሱት ስፈራዎች የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን ሁኔታ አለማወቃቸው አሳስቦናል ብለዋል።

የአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የህወሓት ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው የሠሜን ወሎ እና የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳዳር አካባቢዎች መድረስ አለመቻሉን ነገር ግን የምግብ ዋስትና ችግር ሊኖር እንደሚችል ስጋት መኖሩን ለቢቢሲ ገልጿል።

የኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ማስተባባሪያ ዳሬክተር አቶ ጀምበሩ ደሴ በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው በአጎራባች አካባቢዎች ላሉት የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልፀው፤ በህወሓት ቁጥጥር ሥር ወደሚገኙ ቦታዎች ግን መግባት ባለመቻሉና የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባለመኖሩ ነዋሪዎቹ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እንዳማያውቁ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በዓለም ምግብ ፕሮግራም አማካኝነት ከሰኞ ጀምሮ ወደ ዋግ ኽምራ እና ሰሜን ወሎ ሰብዓዊ እርዳታ መጓጓዝ መጀመሩን ገልጸዋል።

"በሰሜን ወሎ ደላንታ እና ዳውንት ገብተው ሥርጭት ተጀምሯል። በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በሰቆጣ እና አበርገሌም እርዳታ እያደረሱ ነው፤ ከሁለት ወይም ከሦስት ቀናት በኋላ እርዳታ መሰጠት ይጀመራል" ብለዋል ዳሬክተሩ።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከደሃናና ታህን ከሚባሉ ሁለት ወረዳዎች ውጪ ባሉት ወረዳዎች የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንዲገባ መነጋገራቸውንም ዳሬክተሩ ገልጸዋል።

ከወራት በፊት የፌደራል መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ የህወሓት አማጺያን ወደ አጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልሎች ገብተው ጦርነት ከፍተዋል።

ባለፈው ሳምንት በአፋር ክልል ተይዘው የነበሩ ቦታዎች ከአማጺያኑ በመሸነፋቸው ነጻ መውጣታቸውን መንግሥት ያስታወቀ ሲሆን የአማጺው ህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ግን ተዋጊዎቻቸው ከአፋር የወጡት ተሸንፈው ሳይሆን ወደሌላ ሥፍራ እንዲሰማሩ ተፈልጎ እንደሆነ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በአማራ ክልል ሠሜን ወሎ፣ ሠሜን ጎንደርና ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳዳር ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎች አሁንም በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ያሉ ቦታዎች አሉ።

በዚህም ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ አጎራባች አካባቢዎች ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ። ነገር ግን አብዛኞቹ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው አልወጡም።

እስካሁን በእነዚህ አካባቢዎች ስላለው ሁኔታም የተገለጸ የሚታወቅ ነገር የለም።

በአካባቢዎቹ የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባለመኖሩ ነዋሪዎቹ ስለሚገኙበት ሁኔታ ቢቢሲ ለማወቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም።

ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች በአጠቃላይ እስከ 7 ሚሊዮን ሕዝብ ለረሃብ ቀውስ ሊጋለጡ ይችላል ማለቱ ይታወሳል።

ድርጅቱ እንዳለው በሠሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት በአማራ እና አፋር ክልሎች ወደ 1.7 ሚሊዮን ሰዎችን ለረሃብ አደጋ ሲያጋልጥ ወደ 300ሺህ የሚጠጋ ሕዝብን ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬው አፈናቅሏል።

አቶ ጀምበሩ ከሰሜን ወሎ ተፈናቅለው በደሴ ከተማ 233 ሺህ ተፈናቃዮች በዘመድ አዝማድ ቤትና በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ እንደሚገኙ ገልጸው 169 ሺህ ለሚሆኑት ድጋፍ አድርሰናል ብለዋል። የተፈናቃዮች ቁጥር ግን አሁንም እየጨመረ እንደሆነ ተናግረዋል።

እነዚህ ነዋሪዎች በአካባቢው ማኅበረሰብ ትብብር እና በመንግሥት በኩል እርዳታ እየቀረበላቸው ቢሆንም ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች አቅርቦት ግን በቂ ባለመሆኑ "በተለይ ለእናቶችና ለህጻናት ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋል" ብለዋል።

"በሠሜን ጎንደርና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በከፊል፣ በሠሜን ወሎ እና በዋግ ኸምራ መሠረተ ልማቶች በመውደማቸው፤ በጦርነቱ ሳቢያም ነዋሪዎች የዕለት ከዕለት ሥራቸውን ማከናወን ባለመቻላቸውና አርሶ አደሩ እርሻውን መከወን ባለመቻሉ የተረጂዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል" ሲሉ አቶ ጀምበሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተለይ በሠሜን ወሎ እና በዋግ ኽምራ 'የምግብ ዋስትና እጦት' ችግር ሊኖር እንደሚችል ስጋት አለ ብለዋል።

የህወሓት አማጺያን ወደ ክልሉ መግባታቸውን ተከትሎ ከ650 ሺህ በላይ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውንና በአጠቃላይ በክልሉ ከ4 ሚሊዮን በላይ ተረጂዎች መኖራቸውን ዳሬክተሩ ገልጸዋል።

የአካባቢው ተወላጆችሜን ወሎ ስላሉ ቤተሰቦቻቸው ምን ይላሉ?

የወልዲያ ከተማ ነዋሪ የነበረውና አሁን ተፈናቅሎ ደሴ ከተማ የሚገኘው ቴዎድሮስ ወልዲያ ስለሚኖሩ ቤተሰቦቹ ወሬ ከሰማ ከአንድ ወር በላይ ሆኖታል።

መጀመሪያ አካባቢ ከእርሱ በኋላ ተፈናቅለው ከሚመጡ ግለሰቦች ስለሁኔታው መረጃ ይሰማ ነበር። አሁን ግን ይህንንም ከሰማ ሳምንታት እንዳለፉት ተናግሯል።

ቴዎድሮስ እንደሚለው ከኑሮ ውድነቱና ከምግብ አቅርቦት እጦቱ ባሻገር የጤና አገልግሎት ባለመኖሩ የደም ግፊት፣ የስኳር፣ የኤችአይቪ፣ የቲቢ እና ሌላ ህመም የሚከታተሉ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል።

የሠሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ሰላማዊት አያሌው በዞኑ ከ18 ሺ በላይ የስኳር ታካሚዎች፣ ከ20 ሺህ በላይ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ተጠቃሚዎች፣ 1145 የቲቢ ታካሚዎች እንደነበሩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አማጺያኑ "ወጣቶችን ወደ ጦርነት ይማግዳሉ" በሚል ስጋት እርሱ ቀድሞ ከአካባቢው መውጣቱን የሚናገረው ቴዎድሮስ ቤተሰቦቹ በምን ሁኔታ ላይ እንደሆኑ እንደማያውቅ ገልጿል።

"ስለ እነርሱ ሳስብ ነው የምውለው፤ የማድረው፤ ምን በልተው ይሆን? እንዴት ሆነው ይሆን? እያልኩ እንቅልፍ ባይኔ ሳይዞር የሚነጋበት ጊዜ ብዙ ነው" ብሏል።

ቴዎድሮስ እንደሚለው በእድሜ የገፉ እናትና አባቱ ከታናናሽ እህቶቹ ጋር እዚያው ወልዲያ ውስጥ መሆናቸውና አሁን ስላሉበት ሁኔታ አለማወቁ ይበልጥ አስጨንቆታል።

በሠሜን ወሎ ገጠራማ አካባቢ እናቷ እንደሚኖሩ የምትገልፀው ሌላኛዋ ስሟ እንዲገለጽ ያልፈለገች የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ደግሞ እናቷን በስልክ ካገኘች ሁለተኛ ወሯን መያዟን ትናገራለች።

እርሷ እንደምትለው ለወትሮው ብቻዋን የምትኖረውን እናቷን ውሎ ጠንቅቃ የማወቅ ልምድ ነበራት። አሁን ግን ያ የለም። 'እንዴት ሆና ይሆን?' የሚለው ሃሳብ ሰቅዞ ይዟታል።

"እናቴ ቁጡ፣ ፊት ለፊት የምትናገር፣ ብቻዋን የምትኖርበት ግቢ ውስጥ ያለ ፈቃዷ ወፍ ዝር የማታስብል፤ በሌላኛው ጽንፍ ደግሞ ለአንድ እንግዳ ሦስት እንጀራ ከሚገርም ጠላዋ ጋር የምታቀርብ ሴት ናት" ስትል የገለጸቻቸው እናቷ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አለማወቋ አሳስቧታል።

ጦርነቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ያልነካው ሰው የለም የምትለው የባሕር ዳር ነዋሪዋ፤ ጦርነቱ አብቅቶ የእናቷን ድምጽ እንደምትሰማ ተስፋ አድርጋለች።

ይህ በአንዲህ እንዳለ ትናንት ማክሰኞ በደሴ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች በምግብና መድኃኒት እጥረት ለሚሰቃዩ ዜጎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ አደባባይ በመውጣት ጠይቀዋል።

ሰላማዊ ሠልፈኞቹ 'ትኩረት በሰሜን ወሎ ለሚገኙ ወገኖቻችን'፣ 'ወሎ መጠበቅ አይችልም!' 'ወሎ እየተራበ ነው!' 'ፍትሕ በምግብና መድሃኒት እጥረት ለሚሰቃየው የሰሜን ወሎ ሕዝብ' የሚሉና ሌሎች መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

logoBBC rc24 cc2
Copyright © All rights reserved | Marvellous LLC