Welcome

የ'አዲስ:ዜና'ን መተግበሪያ ያውርዱ

የተሻለ የንባብ ተሞክሮ ለማግኘት እና የቅርብ ጊዜ ዜናዎችን ለማየት መተግበሪያውን ያውርዱ።!

Download
Cancel
Image:AddisZena
አዲስ ዜና | Addis Zena
ንብ ባንክ በ2 ቢ. ብር ያስገነባውን ባለ 37 ወለል ህንጻ ዛሬ ያስመርቃል

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በ2 ቢ ብር ያስገነባነውና 37 ወለል ያለውን ግዙፍ ህንጻ ዛሬ ጠዋት የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) እና ሌሎች የክብር እንግዶች በተገኙበት በድምቀት እንደሚመረቅ የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች አስታወቁ፡፡
 ከትላንት በስቲያ ሀሙስ  ከሠዓት በኋላ በአዲሱ የባንክ ህንጻ የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ  ገነነ ሩጋ እና የባንኩ የቦርድ ዳይሬክተሮች ሊቀ መንበር አቶ ወልደ ተንሳይ ወልደ ጊዮርጊስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ባንኩ ከጥቂት ወራት መራዘም በስተቀር በታቀደለት ጊዜ በጥራት ተገንብቶ መጠናቀቁን ጠቁመው፤ በውስጡ 500 ሰው የሚይዝ አዳራሽ ዘመናዊ ጂምናዚየም፣የህፃናት ማቆያ፣ ደረጃውን የጠበቀ ላውንጅ፣ በርካታ የሚከራዩ ሱቆችና ቤተ መፃህፍት እንዲሁም  የስልጠና ማዕከልና ሌሎች መሰረተ ልማቶችም እንደተሟሉለት ተናግረዋል፡፡ ባንኩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ንግድ ስራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) ፊት ለፊት ራስ አበበ አረጋይ መንገድ ላይ የተገነባ ሲሆን ከሚያዚያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ስራ መጀመሩን ከፍተኛ አመራሮቹ አስታውቀዋል፣ህንፃው የአየር ሙቀት መቆጣጠሪያ፣ ዘመናዊ የድምጽ መልዕክት ማስተላለፊያ (public Adress System)፣ ጭስና ሙቀትን የሚለዩ ሴንሰሮች ፣አውቶማቲክ የእሳት ማጥፊያና ውሃ መርጫ፣የታፈነ አየር ማስወገጃ ሲስተም በሁሉም ክፍሎች የተገጠመላቸው ሲሆን በሮቹ ከተለመደው ቁልፍ በተጨማሪ የመዝጊያና መክፈቻ ካርድ እንዳላቸውም ተገልጿል፡፡
ህንፃው ባህላዊውን  የንብ ቀፎና የታታሪዎቹ ንቦች የስራ ውጤት የሆነውን የማር እንጀራ አጉልቶ በማሳየቱ ከዲዛይኑ፣ ከግዝፈቱና የባንኩን ብራንድ ተመርኩዞ ከመሰራቱም በተጨማሪ ልዩ እንደሚያደርገው ሀላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ ዲዛይኑ በእውቁ ኢትዮጵያዊ ኩባንያ አሰፋ ገበየሁ ኮንሰልቲንግ አርክቴክትና ኢንጂነሮች የተሰራ ሲሆን ግንባታውን ያከናወነው ደግሞ እውቁ የቻይናው ጂያንግዡ   ኢንተርናሽናል ኢኮኖሚክና ቴክኒካል ኮርፖሬሽን መሆኑን ሀላፊዎቹ ገልፀዋል፡፡
ተቋራጩ ጨረታውን ሲያሸንፍ ቫትን ጨምሮ በ1.6 ቢሊዮን ብር ወጪ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ሲሆን በህንጻው ዲዛይን ላይ መጠነኛ ለውጥ ተደርጎና ከታች ሜዛኒን ወለል እንዲኖረው በመድረጉና መሰል ምክንያቶች ወጪው ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ማደጉ ተገልጿል፡፡
የዚህ ዘመናዊ ህንጻ መገንባት ባንኩ ለዋና መስሪያ ቤት በየዕመቱ ይከፍለው የነበረውን 30 ሚሊዮን ብር ከማስቀረቱም በላይ በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ አራት ዲስትሪክቶችን ወደዚሁ ህንጻ በማዛወር ለዲስትሪክቶች ይወጣ የነበረውን  ኪራይ ይቀንሳል ያሉት አመራሮቹ፤ በዚሁ ህንጻ ውስጥ ለኮርፓሬት ደንበኞች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት የሚሰጥ “ንብ ፕሪሚየም” ቅርንጫፉን በመክፈት የተሟላ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ስራ የጀመረ ባለ 37 ወለል ህንጻ ባለቤት መሆኑም ፈር ቀዳጅ ያደርገዋል ብለዋል ሀላፊዎቹ፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ከ22 ዓመት በፊት በ1991 ዓ.ም ግንቦት 19 ቀን በ717 ባለ አክሲዮኖች፣በ27.6 ሚ ብር የተከፈለ ካፒታል ተመስርቶ፣ በ27 ሰራተኞች መነሻውን ሾላ ቅርንጫፍ አድርጎ ጥቅምት 18 ቀን 1992 ዓ.ም በይፋ ስራ መጀመሩ ይታወቃል፡፡
ባንኩ በአሁኑ ሰዓት የተከፈለ ካፒታሉን 4.3 ቢሊዮን ብር፣ ተቀማጭ ገንዘቡን 43 ቢሊዮን ብር እንዲሁም የብድር መጠኑን 33 ቢሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 54.6 ቢሊዮን ብር መድረሱም ተገልጿል፡፡ ባንኩ በአጠቃላይ ከ7 ሺህ 400 በላይ ሰራተኞችን በሥሩ እያስተዳደረ  ሲሆን የቅርንጫፎቹን ቁጥር በመላው አገሪቱ 380 ማድረሱንና ከ1.7 ሚ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞቹ ብቁና ቀልጣፋ  የባንክ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

logoAddisAdmass rc16 cc0
Copyright © All rights reserved | Marvellous LLC